
የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር (PHEM) የልህቀት ማዕከልን በይፋ ስራ አስጀምረዋል
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ስርዓቷን ለማጠናከር በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸዋል። የልቀት ማዕከል መመስረት ከአገሪቱ ሰፊ የዲጂታል ለውጥ አጀንዳ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር መቅደስ አክለውም ስኬቱ ተቋማዊ አቅምን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንትን ማሳያ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመለየት፣ ምላሽ ለመስጠት እና ለማስተዳደር የተሻለ ዝግጅት እንዳላት ያረጋግጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን ስራዎች ለማሻሻል የተነደፈ የኤሌክትሮኒክስ እና የዲጂታል መሠረተ ልማት መጀመሩን አስታውቀዋል። የተጠናከረ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ስርዓት የምላሽ ጥረቶችን በማደራጀት እና በጤና ድንገተኛ አደጋዎች ወቅት ቅንጅትን በማሻሻል ረገድ ማዕከላዊ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር የልህቀት ማዕከልን ተግባራዊ ለማድረግ የተከናወኑ ቁልፍ ተግባራትን ዘርዝረዋል። ተቋሙ በተቋማዊ ማጠናከሪያ ላይ የሚያደርገውን ጥረት አፅንኦት ሰጥተው አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት ውጤታማ እና የተቀናጀ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ለማረጋገጥ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ስርዓቶችን ዲጂታል ማድረግን መደገፋቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።